17/08/2022
"የትምህርት ባለሙያዎች በጠንካራ ሥነ ልቦና የታነጸና በሥነ ምግባር የበለጸገ ትውልድ ልትፈጥሩ ይገባል" ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ።
ሑመራ፡ ነሐሴ 10/2014 (አሚኮ) በአማራ ክልል ትምሕርት ቢሮ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ትምሕርት መምሪያ የ2014 ዓ.ም የሥራ አፈጻጻም እና የ2015 ዓ.ም የትምሕርት ዘመን የንቅናቄ መድረክ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በሑመራ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩም የ2014 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2015 ዓ.ም እቅድ ቀርቦ ከትምህርት ባለሙያዎችና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው፤ የሀገር ኢኮኖሚ የሚገነባው በተማረ የሰው ኀይል በመኾኑ በዕውቀት የተካነ እና ብቁ ዜጋ ለማፍራት ልትሠሩ ይገባል ብለዋል።
የዞኑ ማኅበረሰብ ለበርካታ ዓመታት ባሕልና እሴቱን ፣ ቋንቋና ታሪኩን ተነጥቆ የነበረ ሕዝብ በመኾኑ ኅብረተሰቡ ባሕልና ቋንቋውን እንዲያዳብር በትምህርቱ ዘርፍ መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በከፈተው ጦርነት ምክንያት በዞኑ ከ105 ሺህ በላይ መጽሐፍቶች ፣ ከ10 ሺህ በላይ የትምህርት ቤት ወንበሮች ፣ ከ600 በላይ የሥራ ማስኬጃ ኮምፒዩተሮች ፣ ከ1ሺህ 400 በላይ ሰሌዳዎች መውደም ፣ የበጀት አለመኖር እና ከዞን ትምህርት መምሪያ እስከ ትምህርት ቤቶች የባለሙያ እጥረት እና ያሉ ባለሙያዎችም ያለባቸው የልምድ ማነስ በዞኑ የትምህርት አሰጣጥ ሂደት ላይ ጫና ማሳደሩ ተጠቅሷል።
ከነፃነት ማግስት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ትምህርት መምሪያ በአዲስ በመዋቀር በዞኑ ካሉ 197 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 23 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 132 አንደኛ ደረጃ እና 21 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ወደ ሥራ አስገብቷል።
ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዳይርቁና በቂ እውቀት እንዲሸምቱ ባለሙያዎች የበጀት አለመኖርና የግብዓቶች አለመሟላት ሳይገድባቸው ተማሪዎችን በዕውቀት ብቁ ለማድረግ መትጋታቸው በጠንካራ ጎን ተነስቷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲኾኑ በዞኑ የመጽሐፍ እጥረት እንዲቀረፍ ፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች ለትምህርት ተቋማት ትኩረት ሰጥተው ድጋፍ እንዲያደርጉ ፣ የ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በታቀደለት ጊዜ እንዲጀመር እና ተማሪዎች በወቅቱ እንዲመዘገቡ ከማኅበረሰቡ ጋር የንቅናቄ መድረክ እንዲፈጠር ጠይቀዋል።
ከውይይቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ገብረ ማርያም መንግስቴ በዞኑ የወደሙ ትምህርት ቤቶችንና የትምህርት መስጫ ግብዓቶችን ለማሟላት ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥና ተማሪዎች የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ ኀላፊነትን መወጣት ይገባል ያሉት የመምሪያው ኀላፊ በ2015 ዓ.ም በቁሳቁስ እጥረትና በሰው ኀይል አለመሟላት የተዘጉ 67 ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የተማሪዎችን የመማሪያ መጽሐፍ ሙሉ በሙሉ ለማሟላት ከክልሉ ትምህርት ቢሮና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
አስተማሪ ያልቀረጸው ትውልድ ሀገርን መገንባት አይችልምና የትምህርት ባለሙያዎች በስነ ልቦና የነቃና በስነ ምግባር የበለጸገ ትውልድ ልትፈጥሩ ይገባል ያሉት የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ዞኑ ለትምህርት ተቋማት ትኩረት ሰጥቶ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል