09/04/2026
የኢሕአፓ ሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ!
ያስቀመጥናቸው ቅድመ-ሁኔታዎች ቢሟሉ ኖሮ ኢሕአፓ ዐይኑን ሳያሽ በምርጫው ተሳትፎ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከቀጣይ መከራና ዕልቂት ለመታደግ ኢትዮጵያንም ከተደቀነባት የመፍረስ አደጋ ለማዳን የበኩሉን አስተዋጽዖ ያበረክታል ሙሉ ዝግጅትም አድርጎ ነበር። ነገር ግን ገዥው ብልጽግና ፍላጎቱ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ሳይሆን ዛሬም ከቻለ አታሎ፣ አጭበርብሮና ሸውዶ፣ አለዚያም አፍኖና ጨፍልቆ “ተመርጫለሁ ዕወቁልኝ” ለማለት ነው።
በጦርነት፣ መፈናቀል፣ የንጹሀን የጅምላ ግድያ እና እስር የኢትዮጵያ መልኮች በሆኑበት ወቅት የሚካሄድ ምርጫ ለስርኣቱ ንጹሃንን በጅምላ መግደልህን፣ ማሰደድህንና ማሳደድህን፣ ዜጎችን በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት በግፍ ማሰርህን ቀጥል ብሎ መፍቀድናየህዝቡንም ስቃይ ከማስቀጠል የዘለለ ትርጉም አይኖረውም፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በሰራዊት ታጅቦ ምርጫ ለማድረግ መታቀዱም ብልጽግና ለቀጣይ አምስት አመታት በሃይል በስልጣን ላይ ለመቆየት ያለውን ፍላጎት የሚያስረግጥ ነው፡፡
የትግራይ ሕዝብ ለሁለተኛ ጊዜ የማይወከልበት፣ የአማራ ሕዝብ ብልጽግና በጀመረው ጦርነት ወላፈን እየተገረፈ በሚገኝበት እና የማይወከልበት፣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥም በርካታ አካባቢዎች ለአመታት በጦርነት እየተማገዱ ባሉበት እናፖለቲካዊ መፍትሔባልተቀመጠበት የሚካሄድ ምርጫ ትርጉሙ እጅግ አደገኛ እና የአገር አንድነት ከመሰረቱ እንዲናጋ የሚያደርግ ነው እንላለን፡፡
የንጹሃንን ጭፍጨፋ እንዲቆም፣ የኑሮ ውድነቱን የዜጎችን ህይወት እያመሰቃቀለ ስለሆነ በአስቸኳይ ርምጃዎች እንዲገታ፣ የንጹሃን ዜጎችን እስር፣ ማንነት ተኮር እስሮች፣ ወከባዎችና ግድያዎች እንዲቆሙ፣ የዜጎች መፈናቀል፣ ከመኖሪያቸው መፈናቀና መባረር እንዲቆም፣ ሙስና ዓድላዊነትና አግላይነት እንዲወገዱ፣ አምባገነንነት ከሕዝቡ ትከሻ ለማስወገድ የሚሻ ኢትዮጵያዊ በሙሉ ኢሕአፓ አርብ ሚያዚያ 30 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ፣ መቐለ፣ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ሀዋሳ፣ አሶሳ፣ አዳማ እና አምቦ፣ ድሬዳዋ እና ሀረር ከተሞች በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ተገኝቶ በታላቅ መከራ ውስጥ እያለፈ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጎን እንደሚቆም በተግባር እንዲያሳይ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
ብልጽግና ንጹሃንን መግደል እና ማሳደዱን በአስቸኳይ ያቁም!
ሁሉን አቀፍ ሃቀኛ ድርድር ይደረግ!
የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ይፈቱ!
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ - ኢሕአፓ
መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ ፤ ኢትዮጵያ