11/06/2025
ነብዩ ሙሀመድ ﷺ አባታቸውን ከመወለዳቸው በፊት ነበር ያጡት። ውዱ ነብያችን ﷺ በበረሃ ሃገራቸው እናታቸውን ገና በ6 አመት ሳሉ ነበር ያጡት። እናታቸው በህመም ሳሉ በአይናቸው አይተዋል፤ በዛ ልጅነታቸው ይህን አለም ለቃ ስትሄድባቸው ከጎን ሆነው መስክረዋል። አያታቸው ያሳድጓቸው ጀመር። እስከሚችሉት ድረስ ፍቅርና እንክብካቤን አድርገውላቸዋል። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ በ8 አመት ሳሉ አያታቸውንም አጡ። ባለቤታቸው አለም ላይ ካሉ ሰዎች እርሳቸው ዘንድ ተወዳጅ ነበረች። ነገር ግን በከባድ የፈተና ወቅት እርሷንም አጥተዋል።
8አመት ከሞላቸው በዃላ በአጎታቸው ስር ሆኑ። መካ ላይ አጎታቸው ለነብዩ ﷺ ከለላቸው ነበሩ። ነገር ግን ከነብዩ በፊት አለፉ። እንደ አባት ሆነው ያሳደጓቸውን አጎታቸው አሰቃቂ ሞት በአይናቸው አይተዋል። ልባቸው በሀዘን ተሰብሯል። እንደ እናት ሆና ያሳደገቻቸው አክስታቸውን በእጃቸው አፈር አንስተው ቀብረዋል።
ልጆቻቸው ገና ልጅ እያሉ ነው የሞቱባቸው። 4 ወንድ ልጆቻቸውን በህይወት ሳሉ ቀብረዋል። የተባረከ አይናቸው ብዙ አንብቷል። የሚወዷቸው ባልደረቦችና አብሮ አደጎቻቸው ሲሰቃዩና ህይወታቸው ሲያልፍ በህይወት ሳሉ አይተዋል። በድር ዘመቻ ሄደው ሲመለሱ ሴት ልጃቸው ወደ አሄራ መሄዷን ነበር የተበሰሩት። ህይወት ትቀጥላለች። ሌላ ሁለት ሴት ልጆቻቸውን በተባረከ እጃቸው አፈር አልብሰዋል። ምን ያህል ከባድ ነው? ምን ያህል ጥንካሬ ነው?
ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ አንድ ሰሃብይ ስለርሳቸው ሲናገር "ነብዩ ሙሀመድን ﷺ ፈገግታ ተለይቷቸው አይቼ አላውቅም" ብሎ ነበር። ሰለዋቱ ላሂ ወሰላሙ አለይህ!! ምንኛ ያማረ መልካም ባህሪ ነው?
የርሳቸውን ፈለግ የተከተለ በሙሉ አላህ ባጣነው ይተካልን ሰብሩንም ይለግሰን እላለሁ🙏🙏