11/04/2026
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ625 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ መጪውን የትንሣኤ በዓል ምክንያት በማድረግ የክልሉ መንግስት የይቅርታ አዋጁን መስፈርት ላሟሉ 6 መቶ 25 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡
ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት፤ ይቅርታ የተደረገላቸው የሕግ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው መልካም ሥነ-ምግባር የነበራቸው እና በሕግ በተደነገገው የይቅርታ መስፈርትን ማሟላታቸው በክልሉ የይቅርታ ቦርድ ተጣርቶ የቀረቡ ናቸው።
የሕግ ታራሚዎቹ በመደበኛ የይቅርታ ሕግ እና ሌሎች ተጨማሪ መስፈርቶችን የሚያሟሉ ተብለዉ በልዩ ሁኔታ የቀረቡ መሆኑንም አክለው ገልፀዋል፡፡
በዚሁ መሰረት የይቅርታው ተጠቃሚዎች ይቅርታ በማያስከለክሉ ወንጀሎች ተሳትፈው በማረሚያ ቤት የቆዩ፤ ከተፈረደባቸው ሲሶ (1/3) እና ከግማሽ (1/2) በላይ የፍርድ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ እንዲሁም በማረሚያ ተቋማት ስለመታረማቸውና ስለመልካም ባህሪያቸው ማረጋገጫ የቀረበላቸው መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም የይቅርታው ተጠቃሚዎች ከተጎጂ ወገኖች ጋር ታርቀው የእርቅ ሰነድ ማቅረባቸው የተረጋገጠ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ርዕሰ መተዳድሩ የይቅርታው ተጠቃሚ የሆኑ የሕግ ታራሚዎች የይቅርታን እሴት ተላብሰው ሰላም ወዳድ፣ ለሕግ ተገዥና አምራች ዜጋ በመሆን የበደሉትን ህብረተሰብ በማገልግል በልማት የሚክሱ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ህብረተሰቡም በይቅርታ የተለቀቁት የሕግ ታራሚዎች በፈፀሙት ጥፋት የተፀፀቱና በአግባቡ ታርመው የወጡ መሆኑን በመረዳት መልካም እና አምራች ዜጋ ይሆኑ ዘንድ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ መንግስት ይቅርታ ካደረገላቸው 6 መቶ 25 የሕግ ታራሚዎች መካከል:- 5 መቶ 91 ወንዶች እንዲሁም 32ቱ ሴቶች ሲሆኑ፤ ከነዚህም 6 መቶ 23ቱ ከእስር የሚፈቱ እና ቀሪ 2 ታራሚዎች የእስራት ጊዜያቸው የተቀነሰላቸው መሆኑም ታውቋል።
#ርዕሰመስተዳድርጽቤት