12/02/2026
የስንዴው ነዶ፡ የሉዓላዊነታችን እምብርት፣ የብልፅግናችን አዲሱ ምዕራፍ!
የብልፅግና ፓርቲ ለ7ኛው አጠቃላይ ምርጫ ምልክቱ አድርጎ የመረጠው "የስንዴ ነዶ" ይፋ ሆኗል። ይህ ምልክት ተራ ምስል ሳይሆን፣ በላባችንና በጥረታችን የገነባነው አዲሱ የኢትዮጵያ ማንነት መገለጫ ነው። በየቆላውና በየደጋው የሚወዛወዙት ሰፊ የስንዴ ማሳዎቻችን፣ ዛሬ ለፓርቲያችን የድልና የልዕልና ምልክት ሆነው ቀርበዋል።
ይህ የስንዴ ነዶ የመደመር ትልቁ ማሳያ ነው። እያንዳንዱ የስንዴ ዘለላ በአንድ ላይ ተሳስሮ ነዶ እንደሚሆን ሁሉ፣ እኛም ኢትዮጵያውያን በአንድነት ስንቆም የማይበገር አቅም እንደምንፈጥር ያሳየንበት ነው።
የምርታማነት ተምሳሌት የሆነው ይህ ምልክት፣ ከቃላት ባለፈ በተግባር የደረስንበትን የስንዴ ልማት ስኬትና ለነገው ተስፋችን ያለንን ፅኑ መሠረት የሚመሰክር ነው።
ከእንግዲህ ከተረጂነት የመላቀቅ ጉዟችን አይቀለበስም! የስንዴው ነዶ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በምግብ ራስን ከመቻል እንደሚጀምር ትልቅ መልዕክት ያስተላልፋል።
የሌሎችን እጅ ከመጠበቅ ወጥተን፣ የራሳችንን ዳቦ በገዛ መሬታችንና በገዛ ውኃችን አምርተን ለዓለም የምናተርፍበት የልዕልና ዘመን መባቻ ምልክታችን ነው።
ይህ ምልክት የበረከትና የብልፅግና አብሳሪ ነው። በየቤቱ የሚገባው በረከት፣ በየገበሬው ጓዳ የሚታየው ብልፅግና እና በሀገራዊ ደረጃ የምናስመዘግበው ዕድገት በዚህ ነዶ ውስጥ ተሰርተዋል። የስንዴ ነዶው የድካማችን ውጤት፣ የፅናታችን ፍሬ እና ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርሰው የተምሳሌትነት አሻራችን ነው።
ሁላችንም በዚህ አዲስና ተስፋ ሰጪ ምልክት ስር በመሰለፍ፣ ለተከበረችና ለበለፀገች ኢትዮጵያ ቃል ኪዳናችንን እናድሳለን። በስንዴው ነዶ ውስጥ የታሸገው ሉዓላዊነታችን፣ በምርታማነት የሚረጋገጠው ብልፅግናችን ዛሬም ነገም የድላችን አርማ ሆኖ ይቀጥላል።
ድምጽዎን ለስንዴ ነዶ ሲሰጡ፣ ለተራቆተ ተስፋ ሳይሆን ለለመለመ ዕድገት እና ለኢትዮጵያ አዲስ የከፍታ ምዕራፍ እየፈረሙ ነው።