12/09/2023
ኢየሱስ....ይህ ስም እንኳን ከድግምት ከሞት አድኖናል።
***
ኢየሱስ ....ይህን ስም በደንብ ያዙት። በህሊናችሁ አመላልሳችሁ በልባችሁ ዙፋን አስቀምጡት።
ኃያላን የተባሉ ጌቶች ላይ የገነነ፣ነገስታት ላይ ዙፋኑን የዘረጋ፣አምላክቶችን የሰባበረ የጌቶች ጌታ የነገስታት ንጉስ የአማልክቶች አምላክ የሆነ አምላክ ስሙ ኢየሱስ ይባላል።
ከድንግል የተወለደ፣ፍጹም ሰው ሆኖ በጥቂት በጥቂቱ ያደገ፣ሰማይት የማይወስኑት፣መላእክት የሚያመሰግኑት ዙፋኑን በጸባዖት የዘረጋ የማርያም ልጅ ማን ተብሎ ይጠራል ከተባለ "ኢየሱስ" ተብሎ በወርቅ ፊደል ይፃፋል።
እርሱ አጋንንት በመፍራት እና በመንቀጥቀጥ
“ልትሣቅየን ወደዚህ መጣህን? ማቴ8፥29 " እያሉ የሚርዱለት ኃያላንን የሚሰበብር ክንደ ብርቱ እውነተኛ አምላክ ነው።
በድግምት ፣በመተት በሞራ በገላጭ ፣በአስማተኞች፣በጠንቋዮች ፣በሙት መንፈስ ጠሪዎች የሚሰቃዩ ፍጥረትን ከህመም ድካማቸው ያርፉ ዘንድ በአባትነት ቃሉ ወደ እቅፉ የሚጠራ
" የታመሙትንና አጋንንት ያደረባቸውን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤”
— ማር 1፥32" ሲል መጽሐፍ የመሰከረለት ልዑል የሚገለጽበት መጠሪያው ኢየሱስ ይባላል።
እርሱ ገና በሥጋ ሳይገለጥ ነብያት
" ድካማችንን ተቀበለ ደዌያችንንም ተሸከመ" ማቴ 8፥16-17"
ሲሉ ክንደ ኃያልነቱን ትከሻ ሰፊነቱን የመሰከሩለት አምላክ ስም ማን ተብሎ ከተጠየቀ ኢየሱስ ነው በሉ።
“እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን... ቆላ1፥13-14" ተብሎ የተነገረለት በዋጋ ገዢ ቸር አባት ነው እንጅ ለጨለማ ገዢዎች አሳልፎ የሚሰጠን ጨካኝ አባት አይደለም።
በእዚህ ስም አንካሶች ዘለዋል፣ ሽባዎች ቦርቀዋል። እውራን አይተው ሙታን ተነስተዋል።
የዓለም ብርሃን ፣የመሰዋት በግ፣የይቅርታ ግምጃ ፣የቸርነት ባለቤት፣የእውነት መንገድ፣የህይወት መገኛ፣የምህረት ምንጭ የሆነ ስም መጠሪያ ኢየሱስ ይባላል።
በታላቁ የህይወት መጽሐፍ ውስጥ
“እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ማቴ11፥28"
ተብሎ እንደተነገረ እርሱ ሸክማችንን ተቀብሎ ከድካማችን ያሳርፍ ዘንድ የታመነ ጌታ ነው ።
ድግምት እና መዋርት፣አስማት እና መተት በሽምግልና አይለቅም። ቋንጃ በመበጠስ ደሃ በመበደልም አይፈወስም።
ከአባቱ አብ በክብር ሳያንስ፣ከመንፈስ ቅዱስ ህልውና ተካክሎ በተቀመጠው በቅድስት ድንግል ማርያም ልጅ በዳዊት ዘር በኢየሱስ ክርስቶስ እንጅ።
“ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው።”
— 2ኛ ቆሮ 4፥3" የተባለው ቃል የታመነ ነው።
እግዚአብሔር ይመስገን !!!
Kune Demelash kassaye -Arba Minch